የፖለቲካ መርሃ-ግብራችን / Our Program

የፖለቲካ ፕሮግራም
መግቢያ:-

Read in PDF

በዘመናት ታሪኳ፣ ለመላው የዓለም ጭቁን ሕዝብ የነፃነት ዓርማ፣ መመኪያና መከታ ሆና የቆየችው አገራችን ኢትዮጵያ፣ ባለፈው ሃያ አምስት ዓመታት ውስጥ ማለቂያ ወደ ሌለው የዕርስ በርስ ጦርነት እየተነዳች፣ አንድነትዋ ተናግቶ፣ ሕዝቧ ለረሃብ፣ ለሥደትና ለውርደት ተዳርጓል። የታሪክ ጠላቶችዋ ይችን ውብና ባለ ታላቅ ታሪክ አገር፣ ለመቆጣጠር የነበራቸውን ምኞት፤ ከትግራይ ሕዝብ አብራክ በወጡ የህወሀት ፋሽሽቶች ቅንብር ተሳክቶ፣ የባህር በሯን አጥታ የሕዝቧም አንድነት ተክዶ፣ በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ስር በመውደቅ አስከፊ ሁኔታ ላይ ትገኛለች።
የዐማራ ወጣቶች በኢትዮጵያ የተሻለ ሥርዓትን ለማምጣት የከፈሉት የሕይወት መስዋትነት ተክዶ፣ በአገሪቱ ውስጥ ቀደም ብሎ ለነበረው ማሕበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ሁሉ ዐማራውን በብቸኛ ተጠያቂነት ፈርጀው በስፋት ዘመቱበት። እንዲሁም ዐማራው ከሌሎች ወገኖቹ ጋር በአንድነት ሆኖ ለውጭ ቅኝ ገዥዎች አሻፈረኝ አልገዛም በማለት ዕቅዳቸውን ማጨናገፍ መቻሉ፣ በታሪክ ጠላቶቹ የፖለቲካ ስሌት ውስጥ ያልተረሳና የእግር ውስጥ እሳት ሆኖ በመኖሩ፣ ጊዜ ጠብቀው ዘምተውበታል።

ዐማራውን ከኢትዮጵያ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ዑደት ውስጥ በማግለል አዳክሞ ለማጥፋት በተሰላ መንገድ፣ ሕዝብን እርስ በርስ በማጋጨት፣ በዐማራው ላይ የዘር ማጥፋት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። በዚህ ምክንያት እስካሁን ድረስ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር የዐማራ ሕዝብ ባሰቃቂ ሁኔታ እንዲያልቅ ተደርጓል።

በተለያዩ ግዚያት በበደኖ ፣ በአርባጉጉ ፣ በወተር ፣ በአርሲ ፣ በነጌሌ ፣ በአሰቦት ገዳም፣ በአሶሳ፣ ጎንደር በአደባባይ እየሱስ፣ በወልቃይት ፣ በጠገዴ፣ በጌዲኦን፣ በጉጂ፣ በምስራቅ ወለጋ፣ በጅጅጋ፣ በጉሙዝና በቤንቺ ማጂ ዞን፣ በጉራ ፈርዳ ወረዳና በተለያዩ አካባቢዎች ዐማራውን ዒላማ ያረገ ኢሰባዊ ጭፍጨፋ ተካሂዶ ከፍተኛ እልቂት ተፈጽሟል። በሁሉም አቅጣጫ ዐማራው ተከላካይ እንዳይኖረው በማፈን፤ ይህ የግፍ ተግባር ቀጥሎ፤ ከአገሪቱ የተለያዩ ከፍሎች እያፈናቀሉ ከዐማራ የጸዳ አካባቢ እየፈጠሩ ይገኛሉ።

በተጨማሪም ከጎንደር ፣ ከጎጃም ፣ ከወሎና ከሸዋ የሚገኙ ለም መሬቶቹ ከዐማራው ተነጥቀው፤ ለሌሎች በቋንቋ ለደለደሏቸውና ለጊዜው ለሚፈቅዷቸው የአገሪቱ ጎሳዎች ታድለዋል። ከዚህ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ወደ ትግራይ ተከልሏል። አልፎተርፎም ለጎርቤት አገር ለሱዳን ከፍተኛ የቆዳ ስፋት ያለው የአሪቱን መሬት ቆርሶ ለመስጠት እየተዘጋጁ ነው።

በተቀረው ስፍራም ሌሎች ራስ ገዝ አካባቢዎችን በመፍጠር፤ ወደፊት ለሚመሰርቱት የተበታተኑ “የጎጥ መንግስታት“፤ ዐማራው አስጊ ኃይል ሆኖ እንዳይገኝ ለማድረግ ማብቂያ በሌለው ጦርነት ውስጥ የሚከተው የተንኮል ፓሊሲ ተነድፎ ተግባራዊ እየሆነ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የዐማራን ሕዝብ ቆጠራ ውጤት በማዛባት፣ ከዐማራ የፀዳ ቢሮክራሲ ፣ ከዐማራ የፀዱ ከተሞችና ከዐማራ የፀዱ አካባቢዎች በመፍጠር፤ አልፈው ተርፈው ዐማራ አይደለህም በማለት ዐማራውን እራሱን የመከፋፈያ የተለያዩ ስልቶች በመንደፍ ወደ ግጭትና መለያየት እየገፉት ይገኛል።

የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ፋሽስታዊ አገዛዝ፣ ለአገራችን ኢትዮጵያ የተሻለና ለሕዝቧ ጥቅም የቆመ ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያ ደመኛ ጠላቶች ለሆኑት በእጅ አዙር ቅኝ ገዥዎችና በፔትሮ ዶላር ላበጡ የአረብ መንግስታት ዓላማ አሰፈጻሚ ቅጥረኛ ኃይል ነው። በመሆኑም በአገራችን ላይ ጎጠኝነትን በማንገስ፣ በሕዝቧ መካከል ጥላቻና አለመተማመንን በማስፈን፤ ለውጭ ኃይሎች ተንበርካኪ አርጎ እየገዛ ነው። ለታማኝ ታዛዥነቱ ከቅኝ ገዢዎቹ በገፍ በሚያገኘው ያልተቋረጠ ድጋፍ፣ የአገዛዙን እድሜ በማራዘም፣ በሁሉም መስክ የትግራይን የበላይነት ለማረጋገጥ በሚፈጽመው ግፍ የትግራይን ሕዝብ ከቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር የሚያጋጨው ድርጊት በስፋት እየሠራ ይገኛል።
የሃያ አምስት ዓመቱን የሰቆቃ ህይወት መለስ ብለን ስንቃኝ፣ ያለምንም ተከላካይና ተቆርቋሪ ለጥቃት የተጋለጠው የዐማራ ሕዝብ ነው። ከሁሉም እጅግ የሚቆጨው የዐማራ ልጆች በኢትዮጵያ የተሻለ ሥርዓት ለማምጣት ግምባር ቀደም ሆነው ክቡር ሕይወታቸውን የሰጡለት ትግል ውጤቱ፣ ዐማራውንና አገሩን ለማጥፋት የመዋሉ የፖለቲካ ዕንቆቅልሽ ነው።

በዐማራው ሕዝብ ላይ የመከራ ውርጅብኝ ሲወርድበት፣ በወቅቱ የተፈፀመውን ጥቃትና የወደፊቱንም አስጊ ሁኔታ በመረዳት እንደ እሳት አደጋ ተከላካይ ፈጥነው ከተገኙት ከሰማዕቱ መሪያችን ክቡር ፕሮፌሰር አሥራት ወልደየስ ( የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት መዐሕድ) መሪና የትግል አጋሮቻቸው በስተቀር፤ የትኛውም የፓለቲካ ድርጅት ለዐማራው ሕዝብ ህልውናና ተፈጥሯዊ የመኖር መብት መከበር በባለቤትነት ተገቢውን ትኩረት የሰጠ ባለመገኘቱ፣ ዐማራው ግራ በመጋባትና አማራጭ በማጣት የሚፈፀምበትን ማንኛውንም አይነት ጥቃት ሁሉ እንዲቀበል ተገዷል።

ዐማራው ተደራጅቶ ራሱን ከተከላከለ ኢትዮጵያም አለቀላት የሚሉ አዘናጊ አባባሎች በስፋት ይደመጣሉ ። ይህን የሚሉ ወገኖች ዐማራ ባርያ ሁኖ የሚኖርባት ኢትዮጵያ እንደማትኖር የተገነዘቡም አይመስልም። በተለይ የዐማራው ተወላጅ ምሁራን፣ ይህ ሁሉ ግፍ ሲፈጸም፣ ዝምታውና የዳተኝነቱ ምክንያት በጥኑ ሊመረመርና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው።

የዐማራው ስነልቦና ከራሱ አልፎ በኢትዮጵያዊነት ላይ መገንባቱ ዐማራነቱን ከጎጠኞቹና ከታሪክ ጠላቶቹ አዕምሮ ውስጥ አልፋቀውም። በሌላ በኩል ዐማራነቱን ረስቶት፣ ወይንም ሌሎች እንደሚመኙት፣ ጠልቶትና ንቆት እንዳልሆነ ለጠላትም ለወዳጅም ግልጽ ማድረግ የግድ ብሏል።

ከእንግዲህ በዐማራው ህይወት ላይ የሚካሄደው ግፍና ሰቆቃ ማብቂያ ሊደረግለት ይገባል። በሕዝቡ ላይ የሚደርሰው ግፍና በደል የሰው ልጅ ሊሸከመው ወይም ሊታገሰው ከሚችለው በላይ አልፏል። የግልና የወል ነጻነት ተገፏል። ስለዚህ ለህሊናቸው ያደሩ ሰዎች ሁሉ ሊታገሉት ይገባል።
በመሆኑም ይህንን ሕልውና የማስከበር ጥያቄ ባስተማማኝ ሁኔታ ዕውን ለማድረግ፤ የዐማራውን መደራጀት አስፈላጊና ወሳኝ ካደረጉት ዓብይ ምክንያቶች መካከል።
 በዐማራው ህዝብ ላይ ላለፉት ሃያ አምስት ዓመታት በረቀቀ መንገድ አካላዊና ስነልቦናዊ ጥቃት ተፈጽሞበታል። እየተፈጸመበትም ይገኛል። ሰዎች የዜግነት መብታቸው ተገፎ፣ ዐማራ በመሆናቸው ብቻ ከመኖርያ አካባቢዎች በመፈናቀል፤ አሰቃቂ ግድያና ሃብት ንብረት ማጣት ደርሶባቸዋል።
ከዐማራ የጸዱ የመንግስት ተቋማት፣ ከተሞችና አካባቢዎች፣ እየተፈጠሩ ናቸው። በጎንደርና በወሎ በታሪክ የዐማራው መኖሪያ የሆኑ አካባቢዎች በህወሀት በወረራ ተይዘው ነዋሪው ሕዝብ በኃይል ትግሬ ሁን እየተባለ መገደዱ፤ በአጠቃላይ የዐማራው ሕዝብ በመላ አገሪቱ የዜግነት ዋስትና ከማጣቱም በለይ፣ በግልጽና በስውር የዘር ማጥፋት ዘመቻው በስፋት የቀጠለ በመሆኑ።

 የዐማራን ሕዝብ ስቃይና ሰቆቃ ቅድሚያ ሰጥቶ በባለቤትነት ታግሎ ሊያታግል የሚችል የቆረጠ ድርጅት አለመታየቱ። ቢኖርም ለየድርጅቶች የፖለቲካ ፍጆታ ከሚውል ያለፈ ተግባርና ትኩረት ባለመደረጉ። በዚህም ምክንያት በተከሰተው የፖለቲካና ማህበራዊ ቀውስ፣ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለማዳንና ለዜጎች እኩልነትና ለተሟላ ፍትህ መስፈን በሚደረገው ትግል ውስጥ፤ ዐማራው እራሱን በስፋት ከተቃጣበት ጥቃት ተከላክሎ የኃይል ሚዛን የሚያስጠብቅ ወሳኝ ሚና ለመጫወት ይበቃ ዘንድ፣ ብሎም የዐማራው ስነልቦናዊና አካላዊ ደህንነት እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና የመከላከል ብቃቱ ባስተማማኝ ሁኔታ መገንባት እጅግ ወሳኝና በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ሆኖ መገኘት ናቸው።
በአጠቃላይ በግፍ የፈሰሰው የዐማራ ሕዝብ ደም፣ የዐማራ ሕዝብ ሰቆቃና ብሶት፣ የኢትዮጵያ መኖር አለመኖር ጥያቄ ነፍስ አድን የፖለቲካ ድርጅት ወልዷል። “ዳግማዊ የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት“ (ዳግማዊ መዐሕድ) ተመስርቷል።
ታላቁ መሪያችን ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሕይወታቸውን የሰዉለትን ትግል ክስመት ትንሳዔ ለመስጠት ዳግማዊ በሚል የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅትን ከግቡ የሚያደርስ አደረጃጀትና አቅም በሚያገኝበት መልክ ተቋቁሟል።
ኢትዮጵያ ለሁላችንም የጋራ አገራችን ነች። ለኢትዮጵያ እድገትም ሆነ ውድቀት፣ ሃላፊነቱም ሆነ ተጠያቂነቱ የጋራ ነው። የዐማራ ሕዝብ በተናጠልም ሆነ በጋራ ለብቻው የሚያስጠይቀው ምንም ነገር አይኖርም። ስለ አገር መቆርቆር ሰዎች በግልና በጋራ የሚወጡት ብሔራዊ ግዴታ ነው። ዳግማዊ መዐሕድ ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ለሕዝቧ አንድነት መከበር የፀና አቋም አለው።
የሕዝብ አንድነትና ፍቅር የሁሉም የጋራ ፍላጎትና የድርጊት ውጤት ነው ብሎም ያምናል። ዐማራው ለኢትዮጵያ አገራዊ አንድነትና ፍቅር ባለው የማይናወጽ ጽናት የተነሳ ለፖለቲካ ቁማርተኞች ፍጆታ የማዋሉ ተግባር መገታት አለበት።
ዳግማዊ መዐሕድ ከሌሎች አገር አቀፍ ፕሮግራም ካላቸው ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች ጋር በጋራ ጉዳዮች ላይ ለመስራት ዝግጁነቱን ሲገልጽ፤ የዐማራ ሕዝብን ደህንነት፣ ሰላምና ዕድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የሚታገል የፖለቲካ ድርጅት መሆኑን በግልጽ ያሳውቃል።
፻. ራዕይ:-
ሀ. ዳግማዊ የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (ዳግማዊ መዐሕድ ) በትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባርና ተባባሪ ጎጠኞች፣ እንዲሁም በታሪክ ጠላቶቹ ድጋፍ የተቃጣበትን የተቀነባበረ ጥቃት በማክሸፍ፤ ዐማራው በአገሩ የተነፈገውን የዜግነትና የባለቤትነት መብት መልሶ በማረጋገጥ፣ በአገሩ ኢትዮጵያ ውስጥ በፈቀደው ቦታ ሰርቶ የመኖር መብቱን ማስከበር።
ለ. ዳግማዊ የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት፣ በጎጠኛው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ፋሽስታዊ አገዛዝ በዐማራው ላይ የሚፈፀመውን ጥቃትና በደል፣ እስራትና ሞት አስወግዶ፣ ነፃ የሆነ የሕግ የበላይነት የተረጋገጠበት፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞከራሲያዊ መብቶች የተከበረበት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት ያለበት፣ እንዲሁም የአገሪቱ አመራር በግልፅነትና በእኩልነት ፣ ከሕዝብ የሚመነጭና ለሕዝብ ፍላጎት የሚገዛ ሥርዓት በመፍጠር፣ ለምጣኔ ሃብት፣ ለፖለቲካና ለሕዝብ ዕድገት ተባብሮ የሚሰራ ሕብረተሰብ ማየት ናቸው።
፪. ዓላማ:-

ሀ. ከትግራይ ሕዝብ አብራክ በወጣው ፣ የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር ጎጠኛና ፋሽስታዊ አገዛዝ፤ የዐማራው ሕዝብ ታሪክ ተክዶ፣ ያልነበረው እየሆነ፣ የነበረው እየወደመ፣ በአያቶቹና በአባቶቹ አጥንትና ደም በተገነባችው አገሩ ላይ፣ የባለቤትነት መብቱ ተክዶ፣ የአንድነት ተጋድሎ ታሪኩ ውጤት ተንዶ፤ የአገር ጥበቃ መንፈስ፣ የትውልድ የዜግነት ግዴታና በትውልድ የወረሰው የጀግንነት ስሜት እንዲከስም የሚደረገውን አሠራርና ሂደት ለማስቆም ይታገላል።

ለ. ዐማራው ለታሪኩና ለብሔራዊ ደሕንነቱ መከበር በቁርጠኝነትና በፅናት እንደሚታገል፤ ለወዳጅም ለጠላትም እያበሠረ፣ የዐማራው አገር ኢትዮጵያ፤ የዐማራው ካርታም፤ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በእኩልነት የሚጋሩት የኢትዮጵያ ካርታ መሆኑን በርግጠኝነት ያረጋግጣል። የዐማራው ሰንደቅ ዓላማም ፣ ከራሱ አልፎ ለዓለም ጭቁን ሕዝብ የነጻነት ጮራ ምልክት የሆነችው፣ በአረንጓዴ ፣ ቢጫና ቀይ ሕብረ ቀለም ያሸበረቀችው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰንደቅ ዓላማን፤ በክብርና በኩራት እያውለበለበ፣ ህልውናውን ለማስከበር ይታገላል።

መ. የዐማራውን ሕዝብ አብሮነት በማጠናከር፣ ደህንነቱን፣ መብቱን፣ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞቹን ማስከበር። በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ሕዝብን አንድነት በእኩልነት መሰረት ላይ በሕብረት ለመጠበቅና የጋራ አገራችንን ሉዓላዊነት ለማስከበር ቁርጠኝነት ካላቸው ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር በአንድነት ይታገላል።

ሠ. በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት አረመኔዓዊ ዘመቻ ለማስቆም፤ ዳግማዊ መዐሕድ በአገር ውስጥ ዐማራው ተደራጅቶ በተቀነባበረ መንገድ ራሱን ከጥቃት ሊከላከል የሚችልበትን ሁለንተናዊ አቅም ባለቤት እንዲሆን ወቅቱ የሚጠይቀውን ሁሉ በማሟላት የተጠናከረ የማደራጀት ተግባር ይሰራል። በውጪው ዓለም የሚገኘው የዐማራ ተወላጅ በውጭ ቢሮ አማካኝነት ይደራጃል። ዳግማዊ መዐሕድ የውስጥና የውጭ ኃይሉን በማቀናበር ለተሟላ ውጤታማነት ይሰራል።

ረ. መረጃ ለአንድ ሕብረተሰብ ዕድገትና ደህንነት ወሳኝ ሚና ሰለሚጫወት፣ የትግሉን የመስዋዕትነት ክብደት ለመቀነስና የድሉን ጊዜም ለማፋጠን ይቻል ዘንድ፣ በዐማራ ሕዝብ መካከል የመረጃ ስርጭት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመገንባት ዳግማዊ መዐሕድ ቅድሚያ ከሚሠጣቸው ተግባሮቹ ውስጥ አንዱ ነው።
ዐማራው ዕውቀትና ዕውነት ላይ መሰረት ያደረገ መረጃ ተጠቃሚ እንዲሆን፣ የራሱ የሆነ የተሟላ የማህበራዊ የመረጃ አውታርና የብዙሃን መገናኛ ግልጋሎት ባለቤት ማድረግ።

፫. ዳግማዊ መዐሕድ የሚከተላቸው መሠረታዊ መርሆዎችና ዕሴቶች:-
ከዚህ በታች የቀረቡት መርሆዎችና ዕሴቶች ከሊብራል ዲሞክራሲና (የግለሠብ መብት፣ በውድድር ላይ የተመሠረተ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ) ከስምምነት ዲሞክራሲ የተለቀሙ ናቸው።
ሀ. የግለሰብ ነፃት ፦
የሰብዓዊና የዲሞክራሲያ መብቶችን ያከብራል። ዜጎች ቋንቋቸውን የመጠቀምና የማሳደግ፣ ባህልን የማዳበርና እምነትን፣ ልማድን፣ ሰነስርዓትን ተግባራዊ የማድረግ መብት አላቸው። የቡድን እና የጋራ መብቶችን እንደ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የሙያ ማሕበራትና የመሳሰሉ የስብስብ መብቶችን ያከብራል።
ለ. ግንኙነቶች:-
በግለሰቦች መካከል፣ በቡድኖች መካከል፣ በግለሰብና በቡድኖች መካከል ያሉ ግንኙነቶች ተነቃናቂና ተለዋዋጭነታቸውን በመገንዘብ ሚዛናዊና እድገትን አመላካች እንዲሆኑ፣ መብት ከሃላፊነት ጋር መተሳሰር እንዳለበት ዳግማዊ መዐሕድ ያምናል። ታማኝነት፣ ሃቀኝነት፣ ትክክለኝነት፣ ግልጽነት፣ ተጠያቂነት፣ ምላሽ ሰጭነት፣ ተቆርቋሪነት፣ መልካም አርአያነት የመሳሰሉ ኃላፊነቶችን መብት ከማስከበር ጋር ትስስርነት እንዳላቸው ይገነዘባል። በተግባር ላይ እንዲዉሉም ያለማቋረጥ ጥረት ያደርጋል።
መ. አንድነት በልዩነት:-
በተለያየ ቋንቋ ሃይማኖትና ባህል ላሸበረቀ ህብረተሰብ የማንነቱ መገለጫ በመሆኑ ዳግማዊ መዐሕድ የመጠቀም መብታቸውን ያከብራል። አንዱ በሌላው ላይ ተጽዕኖና አድልዎ እንዳያደርግ ይታገላል። ሕብረተሰቡም ጥብቅ በሆነ የአንድነት መሠረት ላይ እንዲቆም ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል።
ሠ. ዲሞክራሲይ ;-
የብዙሃን መንፈስ የተንፀባረቀበት የአስተዳደር ሥርዓት ከሕዝብ፣ በሕዝብ ለሕዝብ የተመረጠ እንደመሆኑ ማንኛውም ሰው ራሱን በሚነካ ውሳኔ ላይ ሃሳብ የመስጠት መብት እንዳለው ዳግማዊ መዐሕድ ያምናል። ግለሰቡ የመምረጥም ሆነ የመመረጥ፣ ሃሣብ የመስጠትና የመተቸት (በመንግስት፣ በሥራ ቦታ ፣ በአካባቢና፣ በብሔራዊ ደረጃ) መብቱ የተከበረ ነው።
ረ. አሳታፊነት፣ አሰባሳቢነት:-
ዳግማዊ መዐሕድ ሕዝቡ በፖለቲካ፣ በምጣኔ፣ በማሕበራዊ፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ ግንዛቤዎች በባለቤትነት መንፈስ ሙሉ ተሳትፎ ያለው ዋነኛ ኃይል መሆን አለበት ብሎ ያምናል።
ሸ. የጋራ ጥቅም :-
ዳግማዊ መዐሕድ ለአንድነት ጥቅም የወል ተግባር ለህልውና እና ለወደፊት ደህንነት ወሳኝነት እንዳለው ስለሚያምን ለተግባራዊነቱ ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል።
ቀ. የትግል ስነስርዓት :-
ታታሪነትና ግልፅነት ለለውጥ እንዲሁም ለዕድገት አስፈላጊ ጠባዮች ናቸው። የግለሰቦችንና የቡድኖችን ተሳትፎ፣ ገንቢ ትችቶችን ለመቀበል፣ አሳታፊና አሰባሳቢ ለሆነ ስርዓት ሰላማዊ ትግል ውጤታማ ነው። ከዚህ በላይ የተገለፁትን አመላካች ነጥቦች ለማይቀበል ፈላጭ ቆራጭ ለሆነ ስርዓት፤ የሕዝብ አመፅ እስከ ጠመንጃ ማንሳት ድረስ እንደሚሄድ ዳግማዊ መዐሕድ ይገነዘባል። አስፈላጊነቱንም ይቀበላል።
በ. እኩልነት :-
ዳግማዊ መዐሕድ እያንዳዱ ሰው ተፈጥሮዓዊ እኩልነት ስለአለው በጎሳ፣ በቀለም፣ በትምህርት፣ በሀብት፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በአመለካከት ወዘተ ላይ የተመሰረተ አድልዎን አይቀበልም።
ተ. የሕግ የበላይነት :-
ባለስልጣኖች፣ የመንግስትም ሆነ የግል፣ ሰራተኞች፣ እንዲሁም ማንኛውም ዜጋ በሕግ ፊት እኩልነታቸውን ዳግማዊ መዐሕድ ያምናል። የየትኛውም አካል ይሁን ማንኛውም ግለሰብ ለሕግ የበላይነት ተገዥ ነው።
በገጠርና በከተማ በትምህርት፣ በሀብት፣ በኑሮ ሁኔታ ወዘተ ያሉ ልዩነቶችን ለማጥበብ እቅድና ጥረት ያስፈልጋል። አቅሙ ካላቸው ዜጎች የሚሰበሰበውን ታክስና ቀረጥ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በሥራ ላይ በማዋል ኃላፊነትን መወጣት ይቻላል።
በዳግማዊ የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት እምነት የመናገር፣ የመፃፍ፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት፣ ነፃነት ከተጠበቀ የሕግ የበላይነት ከተከበረ፣ ሕዝቡ በመንግስት ላይ ቁጥጥር የሚያደርግበት ሥርዓት ከተዘረጋ፣ የስልጣን ክፍፍል (ሕግ አውጭ፣ ሕግ ተርጎሚ፣ ሕግ አስፈፃሚ ) ሚዛናዊነቱን መቆጣጠር ከተቻለ፤ የግል ሀብት ባለቤትነትና የኤኮኖሚ ነፃነት ከተረጋገጠ፤ ውሃ፣ መብራት፣ የብዙሃን መገናኛ፣ ጤና ጥበቃ፣ ትምህርት፣ ሥራ ለሰው ልጅ አስፈላጊ ነገሮች በመሆናቸው ፣ ለተጠቃሚው ዝግጁነታቸው ከተረጋገጠ፣ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች መድረስ ከተቻለ፣ የአገር ድንበርን የሚያስከብር ጠንካራ የመከላከያና ከሕዝቡ ጋር የተስማማ ሰላምና ፀጥታን የሚያስከብር የፖሊስ ኃይል ካለ፤ በችሎታውና በጥረቱ ፈጣን እድገት የሚያሳይ ከራሱ ጋር የታረቀ በአንደነቱ ኮርቶ ደስተኛ የሆነ ህብረተስብ መመስረት እንደሚቻል ዳግማዊ መዐሕድ በጥብቅ ያምናል። ይህንንም ዕውን ለማድረግ ያልተቆጠበ ጥረት ያደርጋል። የዐማራ ሕዝብ ህልውናውን አረጋግጦ አገሩንም ይታደጋል።

፬. ዳግማዊ መዐሕድ የውጭ ግንኙነቶች መመሪያ:-
ሀ. ዳግማዊ መዐሕድ ከማንኛውም የውጭ መንግሥት ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ፣ ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብር በእኩልነትና በጋራ ጥቅም ላይ ተባብሮ መስራት የሚያስችል የውጭ ፖሊሲ ይደግፋል።

ለ. የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ብሔራዊ ጥቅምን እስካልተጋፋ ድረስ የዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ስምምነቶችንና ውሎችን እንዲከበር ይታገላል።

መ. የሰው ልጅ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የማክበር ድንጋጌዎችን፣ ቻርተሮችንና ስምምነቶችን ያከብራል።

ሠ. ለዓለም ሠላምና ዲሞክራሲ ከቆሙ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋሞች ጋር በመተባበር የጋራ ጥቅሞችን የሚያስከብር መርህ ይከተላል።

ረ. በሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባት፤ የመከባበር፣ የመተሳሰብ፣ የሰላም፣የትብብርንና የጋራ ዕድገትን የሚያጠናክር መርህ ይደግፋል።

ሸ. በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ የውጪ ንግድ ግንኙነቶችን ያበረታታል።

የዐማራ ነገድ የተሰነዘረበትን ጥቃት በአንድነት ይመክታል !!!

መጋቢት ፪ሺ፰/ March 2016