ከአማራዊነት በፊት ኢትዮጵያዊነት ይቅደም ለሚሉ አንዳንድ አማራዎች የተወሰኑ ነጥቦች ማንሳት እፈልጋለሁ፡-

ይነበብ
~~~~~
ከአማራዊነት በፊት ኢትዮጵያዊነት ይቅደም ለሚሉ አንዳንድ አማራዎች የተወሰኑ ነጥቦች ማንሳት እፈልጋለሁ፡-
1. የአንድነት ደጋፊ የሆኑ የአማራ ምሁራንና አክቲቪስት ነን የሚሉ ግለሰቦች ነባራዊ ሀቁን የተረዱ አይመስሉም፡፡ ከሌላዉ ብሄር በተለዬ አማራ ለኢትዮጵያዊነት ራሱን መስዋዕት ማድረግ አለበት የሚሉ (የአማራን ህዝብ ጥቅም ለሌላዉ ብሄር ጥሎሽ የሚያቀርቡ) ናቸዉ፡፡ ይህ ግብዝነት ይባላል፡፡ እነዚህ እንደ አበበ ገላዉ እና ታማኝ በየነ (ለጊዜዉ ራሳቸዉን ያጋለጡ የዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች) ያሉ ግለሰቦች ያልተረዱት ነገር ቢኖር፣ አማራዉ እንኳን አሁን አቅም በሌለዉና እንዳይኖረዉ በየአቅጣጫዉ በተዘመተበት ሰዓት፣ ከዚህ በፊት ለኢትዮጵያ አንድነት ለከፈለዉ መስዋዕትነትም ቢሆን ከምስጋና ይልቅ፣ እጁ አመድአፋሽ ሆኖ፣ እንደ ባለዕዳ እየታዬ ይቅርታ ይጠይቅ የሚባልበት ጊዜ ነዉ፡፡ ስለዚህ አማራ በአማራነቱ ብቻ ይዳራጃል፡፡
2. አበበ ገላዉ፣ ታማኝ በየነ እና ሌሎችም የአንድነት አቀንቃኝ አማራዎች (እነሱ አማራ አይደለሁም ጎጃሜ፣ ጎንደሬ፣ ወሎዬ፣ ሸዋ ነኝ ነዉ የሚሉት) በዕድሜ ስለገፉ እንጂ በአሁኑ ሰዓት ያለዉ 65% የአማራ ህዝብ እድሜዉ ከ24ዓመት በታች (ማለትም ህወሀት አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ የተወለደ) ነዉ፡፡ ወያኔ ሲገባ ከ 10ዓመት በታች እድሜ የነበራቸዉን ስናጠቃልል ወደ 80 በመቶ የሚሆነዉ ህዝብ እኮ አማራ ክልልን እንጂ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር አይደለም የሚያዉቁት፣ “ይህ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነዉ” ወይም “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በግብጽ አቻዉ 3 ለ 0 ተሸነፈ” ሲባል ቅስም ሰባሪ የሆነ ዜና እየሰሙ ነዉ፡፡ አሁንኮ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል መፈክር የለም፡፡ አሁንኮ አማራ እንደ ኋላቀር፣ ድሀ፣ መሪ የሌለዉ፣ አርሶ ለገበያ ለማቅረብ ብቻ የሚመሳለቸዉ ብዙ ብሄሮች አሉ፡፡ አማራኮ ተንቋል፡፡ ስለዚህ በአንድነት ተደራጅቶ ራሱን ማደስ አይችልም፡፡ የራሱን ታታሪ ህዝብ፣ የተማረ ሀይል፣ እና ለም መሬት ይዞ፣ የራሱ ስትራቴጂ ኖሮት፣ ራሱን በኢኮኖሚ አሳድጎ፤ ታስፈልገናለህ ተብሎ ነዉ ኢትዮጵያዊ መሆን ያለበት፡፡ እንደ አንድ ግዛት እንጂ የግዞተኞች መሬት አይሆንም፡፡
3. የአንድነት አራማጆች አማራ በአማራነቱ ሲደራጅ “ወያኔ በቀደደዉ ቦይ” ገባችሁ ማለት ነዉ ይላሉ፡፡ ነገር ግን፣ በእኔ አስተያየት እነዚህ የአንድነት አቀንቃኞች ናቸዉ ወያኔ ከቀደደዉ ቦይ ዝንፍ ሳይሉ እየፈሰሱ የሚገኙት፡፡ ምክንያቱም “ወያኔ በቀደደዉ ቦይ” ማለት ወያኔ ከነዚህ ህዝቦች Expect የሚያደርገዉን ማድረግ ማለት ነዉ፡፡ የወያኔ Expectation ደግሞ አማራዉ አንድነት ላይ የሚያሳየዉ ግትር አቋም እና ኦሮሞዉ ነጻ ሀገር ለመሆን የሚያሳየዉ ፍላጎት ናቸዉ፡፡ ለነዚህ ሁለት ተቃራኒ ጉዳዮች ወያኔ ተፈትኖ የተረጋገጠ መድሀኒት አለዉ፡፡ አማራዉን ትምክተኛ እይለ፣ ኦሮሞዉን ደግሞ ጠባብ እያለ ከሁሉም ብሄሮች ጋር ለማጣላት ይጥራል፡፡ ነገር ግን የወያኔን አከርካሪ የሚሰብረዉ ስትራቴጂ፣ አማራ በአማራነት ተደራጅቶ ከዚያ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሰራ፤ እንዲሁም ኦሮሞ በኦሮሞነት ተደራጅቶ ለኢትዮጵያ አንድነት ሲሰራ ነዉ፡፡ አማራ ቅድሚያ ለራሴ ከዚያ የህዝቦችን ሁኔታ አይቼ ለኢትዮጵያ ካለ፣ ኦሮሞ ራሴን ነጻ እድርጌ በጀግኖቼ ደም ተከብራ ለኖረችዉ አገርም ነጻነት እታገላሉ ካለ ያኔ ሁሉ ነገር ያበቃል፡፡ ምክንያቱም የወያኔ ስራዓት የተንጠለጠለዉ፣ አማራ አንድነት እያለ፣ እንዲሁም ኦሮሞ ልገንጠል እያለ በሚያደርጉት የገመድ ጉተታ ነዉ፡፡ ምናለ በሉኝ ከትቂት ሳምንታት ወይም ወራት በኋላ የወያኔ ቴሌቪዥን “የትምክት ሀይሎች የሚያሳዩት የጠባብነት አዝማሚያ ለስርዓቱ አደጋ ነዉ” ማለት ይጀምራል፡፡ የጀርመኑ ኦቶ ቮን ቢስማርክ እኮ ያለዉ– “Politics is the art of the possible” ነዉ፡፡ የታማኝ እና የአበበ ፖለቲካ ግን “Politics is the art of forming a utopian society” ይመስላል፡፡ ያ ደግሞ በአንድ ሺ ዓመት እንኳ የሚሆን አይመስልም፡፡
4. አንዴ ካፌ ዉስጥ ቁጪ ብዬ ቡና እየጠጣሁ እያለ ሁለት ወጣቶች መጥተዉ አጠገቤ ተቀመጡ፡፡ አስተናጋጇ ስትመጣ አንዱ ሻይ-ቡና ስፕሪስ አለ፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ማኪያቶ አለ፡፡ ልጂቷ እንደ-መሄድ ስትል ስፕሪስ ያዘዘዉ ልጅ “ማኪያቶዉ ጠቆር ይበል” አለ ጮክ ብሎ፡፡ እስካሁን ይገርመኛል፡፡ የአማራ ምሁራን ለእኔ እንደዚ ስፕሪስ እንዳዘዘዉ ልጅ ናቸዉ፡፡ ሶማሌ ክልል መገንጠል እፈልጋሉ ካለ ቀድሞ ቡራከረዮ የሚለዉ አማራዉ ነዉ፡፡ ግንኮ ከአማራዉ ህዝብ 99.9% በህይወት ዘመኑ የሶማሌን ክልል በእግሩ ረግጦ አያዉቅም፡፡ ሶማሌ ክልል ለስራ እና ለጉብኝት ከሄዱት አማራዎች ይልቅ ሶማሌዎቹን አትሄዱም ብሎ በጦርነት የወደቀዉ አማራ ይበልጣል፡፡ ደሞምኮ ቢገነጠል ድንበሩ ለጥቃት የሚጋለጠዉ ኦሮሞዉ እንጂ አማራዉ አይደለም፡፡ ኦሮሞዉ ግን እኔ እያለሁ ሶማሌ አይገነጠልም የሚል አቋም ኖሮት አያዉቅም፡፡ እና የአማራ ልሂቃን ለጉራ፣ ለኩራት፣ አባቶች ያቆዩት አገር እያላችሁ ወገንህን አታስጨርስ፡፡ ከዛ ይልቅ ለአማራ አንድነት ስሩ፣ ካልቻላችሁ ዝም በሉ፡፡ እንዲያዉም አንዱ ስህተት ህዝቦችን በጉልበት ማቆየቱ ነዉ፡፡ ኤርትራን ለማቆየት፣ ኦነግን ለማድከም፣ ሶማሌን ለማቆየት፣ ትግራይን ከጣልያን ለማዳን እና ባድመ ላይ የሞተዉ አማራ እና የፈሰሰዉ ገንዘብ የአማራን መሬትና ህዝብ ለማልማት ቢዉል ኖሮኮ በአሁኑ ሰዓት ከነ ግብጽ፣ ከነሊቢያ ያነሰ እድገት አይኖረንም ነበር፡፡ አሁንም እንድነት የሚፈልግ ካለ አብረን እንኖራለን (ነገር ግን የአማራን ጥቅም አስከብረን፣ የአማራን ገበሬ ህይወት ቀይረን)፣ ካለዚያ የአማራን ህዝብ ጥቅም በአንድነት ሰበብ ጥሎሽ አያቀረብን መኖር አንችልም፡፡
5. በቅርቡ አንድ ሪፖርተር ላይ የሚሰራ ጋዜጠኛ እኔ ትግሬ ነኝ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ብሎ ጽፎ ነበር፡፡ ትግሬ፣ አማራ፣ ኦሮሞ የሚባል ማንነት እንጂ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም ብሎ ነበር፡፡ ጃዋር ሞሀመድም እኔ ኦሮሞ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም ብሎ ነበር፡፡ መለስ ዜናዊም “እንኳን ከዚህ ከወርቅ ህዝብ ተወለድሁ” ያለዉ የትግራይን እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ አይደለም፡፡ ስለዚህ አማራ ከአማራ በፊት ኢትዮጵያዊ ነኝ ቢል የሚጠብቀዉ ያልተደራጀ መንጋ መሆን ነዉ፡፡ ኪሳራዉም ብዙ ነዉ፡፡ የመለስ ዘመነኞች የተሸዱትን በድጋሜ ይሸወዳል፡፡ እንዲያዉም በዚያ ዘመን በአንድ ኢትዮጵያ የሚያምኑ ብዙ ትግሬዎች፣ ኦሮሞዎች ፣ ወላይታዎች፣ አፋሮች የነበሩበት ነዉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ግን ኢትዮጵያዊ አንድነትን ቅድሚያ የሚሰጥ ብሄር የለም፡፡ ከአንዳንድ ዲያስፖራ አማራዎችና ፖለቲካ ከማይገባቸዉ ጨዋ ሰዎች በስተቀር፡፡ የሀገር ቤቱ አማራ (በአማራ ክልል ያለዉም ሆነ ከዚያ ዉጪ ያለዉ) ኢትዮጵያዊ አንድነት ከአማራነት በላይ ቅድሚያ እሰጣለሁ የሚል የሚኖር አይመስለኝም፡፡ እኔ አዲስ አበባ ዉስጥ እየኖርሁ፣ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆኘ እያለሁ እንኳ ኢትዮጵያዊነት አይሰማኝም፡፡ ምክንያቱም መታወቂያዬ አማራ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይልም፡፡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም ኢትዮጵያዊ በሚለዉ ሳይሆን እንደብሄራቸዉ ይቀራረባሉ፡፡ ስለዚህ አማራዉ ቅድሚያ በአማራነት ተደራጅቶ ከዚያ ለኢትዮጵያዊነት ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር በተለይ ከኦሮሞዉ ጋር መተባበር እና መደራደር ይጠብቀዋል።
6. በኃይለ ሥላሴ ዘምን ዘመኑ ኋላቀር በመሆኑ ሁሉንም ብሄሮች ለብሄር-ትግል ለማደራጀት አይመችም ነበረ፡፡ እንዲሁም ሁሉም ኢትዮጵያ ብሄሮች አንድ የሚያደርግ ነገር ነበራቸዉ፡፡ ይኸዉም አገሪቱ የንጉሱ ፋብሪካ ስትሆን ሁሉም ህዝቦች ደግሞ እንደ ወዛደር ነበሩ፡፡ አሁን ግን ሁሉም ነገር ተቀይሯል፡፡ ያለዉ የመከፋፈል ችግርም ቀላልና የሚጠገን አይደለም፡፡ ያለዉ ከ80 በላይ ብሄር ስለራሱ ነዉ የሚያስበዉ፡፡ ወጣቱም እየተማረ ያደገዉ ይህንኑ ነዉ፡፡ ስለዚህ በአማራ ፍላጎት ብቻ አንድነት ማምጣት አይቻልም፡፡አሁን ያለዉ ፈታኝ ችግር እንደ simultaneous equation አይደለም፣ ያሉት variables ከ80 በላይ ናቸዉ፡፡ ነገር ግን፣ አማራ የማይመራዉ (የአማራን ጥቅም እንደሁልጊዜዉ የማያስጠብቅ) የአንድነት መንግስት መመስረት ላይከብድ ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ጥያቄዉን ለማቅለል የአንድነት ሀይሎች boundary condition ሊያሰቀምጡ ይችላሉ፡፡ እናም ሁሌም የፖለቲካ ድርጅቶች ኢላማ የሆነዉን ህዝብ መስዋዕት በማድረግ Assume there is no Amhara ብለዉ ሊነሱ ይችላሉ፡፡
7. በፊዚክስ ትምህርት ዉስጥ Entropy (it is a measure of disorder) የሚባል ንድፈ ሀሳብ አለ፡፡ Entropy ሁሌ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ ለምሳሌ አንድ አሞሌ ጨዉ በአንድ ገንዳ ዉሀ ዉስጥ ብትጨምሩት፣ ጨዉ እየሟሟ ይሄዳል፣ ሞሎኪዉሎቹ እየተራራቁ ይሄዳሉ እንጂ የሚሰበሰቡበት አጋጣሚ የለም፡፡ አንድ የጋለ ብረት አንድ ክፍል ዉስጥ ብታስቀምጡ ሙቀቱ በክፍሉ ዉስጥ ይሰራጫል እንጂ የክፍሉ ሙቀት ተሰብስቦ ብርት አይሞቅም፡፡ የተፈጥሮ አካሄዱ መበታተን ነዉ፡፡ ይህን ንድፈ ሀሳብ ወደ ህብረተሰባችን መስተጋብርና ፖለቲካ አዉርደን ብናየዉ የኢትዮጵያ ብሄሮች ከዚህ በኋላ እንደድሮዉ እንድ ነን ይላሉ፣ ስለ አማራ ጭራቅነት ተነግሮት ያደገ ትዉልድ ስለአማራ ደግነት ያወራል ማለት ዘበት ነዉ፡፡ አብዛኛዉ አማራ ሌሎች ብሄሮች ይጠሉኛል ብሎ አያስብም፡፡ ሌሎች ብሄሮች ስለ አማራ ያላቸዉ አመለካከት ቢነገረዉ እንኳ አይሰማም፡፡ ነገር ግን እዉነታዉ ሌላ ነዉ፡፡ ስለዚህም ነዉ አማራ አንድነት ያስፈልገዋል ራሱን ለመጠበቅ፣ የልማቱ ተካፋይ ለመሆን፣ ባህሉን፣ እምነቱን፣ ትዉልዱን ለማስቀጠል የሚባለዉ፡፡ በተለይ ወያኔ ኢትዮጵያ ላይ ጢባ ጢቤ ከተጫወተ በኋላ በብሄሮች መካከል ያለዉ ያለመተማመን እየጨመረ ነዉ የመጣዉ፡፡ ተመልሰን ወደ ዘር ቆጠራ መግባት ግድ ይለናል፡፡ ይህን የማታምን አማራ አንገትህ ሲቆረጥ ይገባሀል፡፡ የአማራ ዲያስፖራዎች በኢትዮጵያዊነትህ ሻማ ያበሩልህ ይሆናል፡፡ በአማራነትህ ኢላማ ስትሆን ግን ቢያዉቁም አይነግሩህም፡፡ ለአለፉት አርባ አመታት አየተጨቆነ እየተገደለ እንኳን ምንም እንዳልተነካ ሁሉ ተሸፋፍኖ የተኛ እና ያልተደራጀ ህዝብ አሁንም ለህልዉናዉ በሚያሰጋ ሁኔታ ላይ ሆኖ እንኳን የራሷ አሮባት የጎረቤት ታማስላለች አይነት እንዝላልነት በተለይ በተማረዉ እና ከተጎሳቆለዉ የአማራ ገበሬ የተገኙ መሁራን በአዚም መጠቃት ያበሽቃል፡፡ እነዚህን እና የመሳሰሉትን ስታዩ ሚሚ ስብሀቱ “ሪታርድስ” ያለችዉ፣ ሌላዋ “አህዮቹ ሮቦሹኝ ኡኮ” ያለቸዉ፣ እንዲሁም እንዲሁም አባይ ጸሀየ “ኳላ ቀሮች” ያለዉ፣ እዉነታቸዉን ይሆን እንዴ እላለሁ፡፡ መቸም የተማረ አማራ ሁሉ ሀያ አምስት አመት ከብዙ ጥቅማ ጥቅም ሁሉ ተገልሎ እንኳን በአማራነት አልደራጂም ካለ ችግር ቢኖር ነዉ እላለሁ (በአሁኑ ሰዓት ያለዉ ምሬት እና መነሳሳት እንዳለ ሆኖ)፡፡
8. በአሁኑ ሰዓት አንድነት ወይም ኢትዮጵያዊነት የሚል አማራ ካለ እሱ የድሮ ዘመን ሰዉ ነዉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ዉስጥ የሚኖር አማራ ስለ ኢትዮጵያዊነት ምንም ስሜት የለዉም፡፡ ምናልባት እንደ አዲስ አበባ፣ ናዝሬት፣ ድሬዳዋ እና ሀዋሳ ያሉ ከተሞች የሚኖሩ አማራዎች አንድነት ሊሉ ይችልሉ፤ ነገር ግን እሾህን በእሾህ እንደሚባለዉ በአሁኑ ሰዓት በአማራነት፣ በኦሮሞነት፣ በሲዳማነት፣ በጉራጌነት ካልተደራጀን ህልዉናችን አደጋ ላይ ነዉ፡፡ እስኪ ታማኝ በየንን እዩት ሀያ አምስት አመት ሙሉ አንድ ኢትዮጵያ ብሎ ያተረፈዉ ነገር ምንድን ነዉ፡፡ ታማኝና መሰሎቹ አቋማቸዉን ካልቀየሩ እንዲሁም አማራ በአማራነቱ ካልተደራጀ ከታማኝ በፊት ቀድመዉ አማራ ክልል የሚገቡት የትግራይ ህዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ትህዴን) አባላት፣ ኦነግ፣ ወይም ሻዕቢያ ናቸዉ፡፡ ከዚያም አበበ ገላዉ “We need Freedom! Mr. X is a dictator.” ለማለት፣ ታማኝ በየነም የአንዱን ባለስልጣን በትግል ወቅትና በስልጣን ዘመን ያደረገዉን ንግግር ኤዲት እያደረገ ኮሜዲ ለመስራት የሚያደርስ መንገድ ነዉ፡፡
9. አንድነት መደራጀት ለጥቃት መጋለጥ ነዉ፡፡ እስካሁን እንዳየነዉ፣ በአንድነት አቀንቃኝ ፓርቲዎች ስር መሰባሰብ (አንድነቱ ትግሬንም ስለሚጨምር) መዳረሻዉ መበታተን፣ እንዲሁም አላማዉ የህወሀት የስለላ መረብ ሆኖ ማገልገል እንደሆነ ሁሉም የአማራ ፖለቲከኞች ያዉቃሉ፡፡ ነገር ግን፣ ዝም ከማለት እየሞቱም ቢሆን ሀቁን መናገር ይሻላል የሚል ስትራቴጂ የአማራን ህዝብ መብትም አያስከብርም ከንቱ ልፋትም ነዉ፡፡
#አማራ_ተጋድሎ
አንድርያስ

Share this post