ከመላው ዐማራ ሕዝብ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ፡፡ መዐሕድ በጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ የስያሜ እና ዓርማ ለውጥ አደረገ፡፡

ከዚህ ቀደም በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በሀገር ውስጥ በህቡዕ ለህግ የበላይነት፣ ለማህበራዊ ፍትኅ እና ለዴሞክራሲ መንሰራፋት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እና ወኔ ሲታገል የነበረው የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) በግንቦት ስድስት ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ የሀገር ፍቅር ቲአትር አዳራሽ ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራት የተውጣጡ አባላት በተገኙበት ጠቅላላ ጉባዔውን አካሂዷል፡፡ በዚህ ጉባዔ ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎች፣ ዞኖች እና ወረዳዎች የተውጣጡ የጉባዔ አባላት የተካፈሉ ሲሆን የተለያዩ ተጋባዥ እንግዶችም ጉባዔውን ታድመዋል፡፡  

ከዚህ ቀደም ለመላው የዐማራ ሕዝብ፣ ለአባላቶቻችን እና ደጋፊዎቻችን በተለያዩ መንገዶች ለመግለፅ እንደሞከርነው መዐሕድ በመንግስት ጥሪ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ሲገባ በምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ መመዝገብ እና መታገል እንዳለበት አቅጣጫ ተሰጥቶታል፡፡ ውሳኔውን ተከትሎም መዐሕድ የመስራች አባላት ምዝገባ፣ ወቅቱን ያገናዘበ የፖለቲካ ፕሮግራም እና ሌሎች ሰነዶች አዘጋጅቶ በግንቦት 6 ቀን ጠቅላላ ጉባዔ ለማድረግ በቅቷል፡፡ ዕለቱ የትግሉ ነፀብራቅ ክቡር ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የአረፉበት 20 ዐመት በመሆኑ የሙት ዓመታቸውን ሀውልታቸው በሚገኝበት የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን እና በጉባዔው አዳራሽ ዘክሯል፡፡

በጠቅላላ ጉባዔው ዕለትም ክለሳ የተደረገበትን የፖለቲካ ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደንብ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የስያሜ እና የዓርማ ለውጥ ያደረገ ሲሆን ጠቅላላ ጉባዔውም በሙሉ ድምጽ ተቀብሎታል፡፡ በዚህም መሰረት ስያሜውን ከመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) ወደ የመላው ዐማራ ሕዝብ ፓርቲ (መዐሕፓ) ቀይሯል፡፡ ከድርጅትነት ወደ ፓርቲነት ሲሸጋገርም ዋና ማዕከሉን አዲስ አበባ በማድረግ ዐማራ በሚገኝባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ በመድረስ ያልተቆጠበ ድጋፉን ለማበርከት ቃል-ኪዳን ገብቷል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትግሉን ሲመሩት የነበሩ ወንድሞችም በጉባዔው ዕለት በአካል ተገኝተው የኃላፊነት ሽግግሩን በሀገር ውስጥ ለሚገኙ ወንድሞቻቸው በሰላም አከናውነዋል፡፡

በዚህ አጋጣሚ መዐሕፓ ለዐማራ ሕዝብ፣ ለአባላቱ እና ደጋፊዎቹ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክቱን ለማስተላለፍ ይወዳል፡፡ በቀጣይም መዐሕፓ የፖለቲካ ርዕዮቱን፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሌሎች ወሳኝ አጀንዳዎቹን ለሕዝብ ይፋ የሚያደርግ ይሆናል፡፡

ፈለገ አስራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!!

የዐማራ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል!!

http://www.aapo2nd.org/2020/wp-content/uploads/2019/05/AAPP-Megilecha-16.05.2019.pdf

Share this post

5 thoughts on “ከመላው ዐማራ ሕዝብ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ፡፡ መዐሕድ በጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ የስያሜ እና ዓርማ ለውጥ አደረገ፡፡