የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) ግንቦት 06 ቀን 2011 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ያካሂዳል!!!


ለመላው የዐማራ ሕዝብ እንዲሁም የመዐሕድ አባላት እና ደጋፊዎች፤
ለበርካታ ዓመታት በውጭ ሃገር ሆኖ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ በሁሉም አካባቢዎች የህግ የበላይነት እንዲሰፍን እና ማህበራዊ ፍትኅ እንዲረጋገጥ የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያበረክት የቆዬው የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) በትግሉ ፋና ወጊ ፕሮፌሰር አስራት ወልደዬስ 20ኛ የሙት ዓመት ቀን ግንቦት 06 ቀን 2011 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤውን በአዲስ አበባ ሊያካሂድ መሆኑን ሲገልፅ በታላቅ ደስታ ነው፡፡
***********
የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ) በ 2010 ዓ.ም በኢትዮጵያ በተገኘው የአመራር ለውጥ መንግስት በውጭ ሃገር ለሚገኙ እና ትግል ሲያደርጉ ለነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ቡድኖች ባቀረበው ጥሪ መሰረት በነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ወደ ኢትዮጵያ የልዑካን ቡድኑን በመላክ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡ እነሆ ከዚያ ቀን ጀምሮ በቁርጠኛ ልጆቹ ትጋት አደረጃጀቱን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በመዘርጋት እና ሕብረተሰቡን በማወያዬት ለዚህ ታላቅ የድል ቀን በቅቷል፡፡
***********
በመሆኑም ሁሉም የዐማራ ሕዝብ፤ የመዐሕድ አባል እና ደጋፊዎች ለዚህ ቀን እንድንበቃ ላበረከታችሁት አስተዋጽኦ ልባዊ ምስጋናችንን እያቀረብን በዕለቱ ግንቦት 06 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ የምናካሂደውን ጠቅላላ ጉባዔ በአካል በመገኘት እና በተለያዩ ሚዲያዎች እንድትከታተሉ በአክብሮት እንጋብዛለን፡፡ የጠቅላላ ጉባዔ አዳራሽ እና ሌሎች ዝርዝር መረጃዎችን በቅርቡ የምናሳውቅ መሆኑን እናሳስባለን፡፡
***********
ፈለገ አስራት የትውልዳችን ቃል-ኪዳን ነው!!
የመላው ዐማራ ሕዝብ ድርጅት (መዐሕድ)
አዲስ አበባ

read in pdf . General Assembly Organization Communique – Statement

Share this post