በሃገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን የሰላም መደፍረስ እና የፀጥታ ችግር በተመለከተ ከመዐሕድ የተሰጠ መግለጫ!


በአሁኑ ወቅት በሃገራችን በብዙ አካባቢዎች የሰላም መደፍረስ እና የፀጥታ ችግሮች እየገጠሙ የህብረተሰቡን በሰላም ተንቀሳቅሶ የመስራት እና የመኖር ህልውና የሚፈታተን ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ምንም እንኳን በተወሰኑ የፌደራል እና የክልል ተቋማት በመንግስት እየተተገበሩ የሚገኙ ሪፎርሞችን እና ለውጦችን ብናደንቅም በሃገሪቱ የተከሰተው ችግር ግን አሁን በሚደረገው ለውጥ ብቻ ከዚህ ግባ የሚባል መሻሻል ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ እንኳን ስፋት ያለው ሪፎርም ተደርጓል እየተባለ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በተቋሙ የሚታዬው የህዝብ ወገንተኝነት እና አድሎአዊ አሰራር ግን እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በተወሰኑ አካባቢዎች አጥፊዎችን እሹሩሩ እያለ በዐማራው ሕዝብ ላይ ሴቶችን እና ህፃናትን ጨምሮ በበርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ አሰቃቂ የሆነ ጭፍጨፋ እየፈፀመ ይገኛል፡፡በጣም የሚገርመው ደግሞ መከላከያው የአንድን በወንጀል ስራ የተሰማራ ለትርፍ የተቋቋመ ድርጅት ለማጀብ ድርጊቱን መፈፀሙ ነው፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በዐማራ ምዕራብ ጎንደር በተለይ ደግሞ በመተማ፣ ገንደ ውኃ፣ ኮኪት፣ ጭልጋ እና አካባቢው የጎንደር ክፍል በመከላለከያ ሰራዊቱ በተፈፀመው አስነዋሪ እና አሰቃቂ ጭፍጨፋ ለሞቱ፣ የአካል እና የስነ-ልቦና ችግር ለደረሰባቸው፣ ለተፈናቀሉ እና አሁንም በጭንቀት እየተሰቃዩ ወይም እየተሰደዱ ለሚገኙ ወገኖቻችን መዐሕድ የተሰማውን ልባዊ ሐዘን ይገልፃል። ችግሩ በተከሰተበት አካባቢ ሕዝቡ የችግሩን መንስዔ እና ስጋቱን አስቀድሞ ሲጠቁም የቆዬ ቢሆንም በመንግስት በኩል እየተሰጠው ያለው ምላሽ አጥጋቢም አይደለም፤ ምላሹም የዘገዬ እና የኃላፊነት ጉድለት የሚታይበት ነው፡፡ በአካባቢው የፖለቲካ እና ማህበራዊ ቀውስ እንዲፈጠር የሚሠሩ አካላትን ከለላ በሚሰጥ እና የማኅበረሰቡን ስጋቶች እና መፍትሔ ጠቋሚነት ያገለሉ እርምጃዎችን መውሰድ ኃላፊነትን መዘንጋት ብቻ ሳይሆን አካባቢው እንዳይረጋጋ ከመፈለግ የሚመነጭ ሴራ ክፍል ነው ብለን እናምናለን፡፡
ይህ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ እንደሆነ መንግስት አልተረዳውም፡፡ ሊረዳው የሚፈልግም አይመስልም፡፡ የክልሉ አስተዳደርም የህዝቡን ስሜት ለማብረድ ጊዜያዊ መግለጫ ከማውጣት በዘለለ ችግሩን ለመፍታት በጥልቀት እና በትኩረት እየሠራ አይደለም፡፡ ይህ ችግር የወያኔ ሴራ እና በቀል ማወራረጃ ኢላማ ነው፡፡ የፌደራል መንግስት ችግሩን የመፍታት አቅም ወይም ፍላጎት ከሌለው የአካባቢው ማኅበረሰብ ችግሩን በተለያዩ ማህበራዊ እና አካባቢያዊ መንገዶች የሚፈታበትን ሂደት ጠንቅቆ ስለሚያውቀው ኃላፊነት ወስዶ ራሱን ይከላከላል።

ስለሆነም የአካባቢው ማህበረሰብ መንግስት ለጉዳዩ እየሰጠው ያለውን አናሳ ትኩረት በመረዳት በከፍተኛ ጥንቃቄ እና መረጋጋት፤ በውይይትና በመመካከር ለመፍታት መዘጋጀት አለበት፡፡ የክልሉ አስተዳደርም ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጠው እየጠየቅን ከአቅሙ በላይ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ የፌደራል መንግስቱን ጣልቃ ማስገባት እንደሌለበት መዐሕድ ያሳስባል፡፡ በዐማራ ሕዝብ ያገባናል የምንል ሁሉ በጋራ በመሆን እና ችግሩን ከስር-መሰረቱ በማጤን የማያዳግም መፍትሔ መሻት ግድ ይለናል፡፡ መዐሕድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሠራ ይገኛል። በመዐሕድ በኩል በአካባቢው ከሕዝባችን ጎን በመሆን ከምናበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ የሚከተሉት ወሳኝ ጉዳዮች ትልቅ ትኩረት እንደሚሹ ለማሳሰብ ይወዳል፡፡

1. ሱር ኮንስትራክሽን በአካባቢው ሲያከናውናቸው ለነበሩ አጠራጣሪ፣ አበጣባጭ እና የሕዝብን ደኅንነት የሚፈታተኑ ተግባራት አሁንም ለተፈጠሩ ቀውሶች በህግ እንዲጠየቅ፡፡ ከዚህ በኋላም የሚያደርጋቸው ማናቸውም እንቅስቃሴዎች በህግ እና በማኅበረሰቡ እውቅናና ፈቃድ ብቻ እንዲሆኑ እንጠይቃለን፡፡ የክልሉ እና የፌደራል መንግስትም ቢሆን ህዝብ የሚሰጣቸውን ጥቆማዎች እንደቀላል ሳይመለከት የሱር ኮንስትራክሽን ድርጅት ከህዝብ በተገኘው ጥቆማ መሰረት ለህግ እንዲቀርብ እና በጥፋቱ ልክ ቅጣቱን እንዲቀበል እንዲደረግ እንጠይቃለን፡፡
2. የሃገር መከላከያ ሕዝብን በእኩልነት እና በህግ ለማገልገል ከተሰጠው ተልዕኮ ውጭ በምዕራብ ጎንደር ገንደ ውኃ እና ኮኪት አካባቢ ላደረሰው የሞት፣ የአካል ጉዳት እና የንብረት ጥፋት በግልጽ ይቅርታ እንዲጠይቅ፡፡ ለተጎዱ ወገኖችም ካሳ እንዲከፍል እንጠይቃለን፡፡ ከዚህም በላይ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዳይመጣ ከሚሰሩት ጋር በድብቅ ተልዕኮ ያላቸው አመራሮቹ በውስጥ አደረጃጀቱ ተሰግስገው እንደሚገኙ በርካታ መረጃዎች እና ማስረጃዎች ስላሉ ለአካባቢው ህብረተሰብ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት ሲባል አካባቢውን ለቆ እንዲወጣ እየጠዬቅን የክልሉ መንግስትም ከአቅም በላይ ባልሆኑ ጉዳዮች ላይ የፌደራል መንግስቱን ጣልቃ ገብነት ይገታ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
3. የፌዴራል መንግስት በመከላከያ አመራር በመስጠት በህዝብ ላይ ጉዳት ያደረሱትን ተሳታፊዎች መርምሮ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ እንጠይቃለን፡፡ መከላከያም እንደ አንድ ትልቅ ሃገራዊ ተቋም ከእንደዚህ አይነት ኃላፊነት የጎደለው እና አድሎአዊ አሰራር ተላቆ ወገኖቹን በእኩል ዓይን በመመልከት ለህዝቡ ሰላም እና ደህንነት መጠበቅ በቅንነት እና በታማኝነት እንዲሰራ እንጠይቃለን፡፡
4. የተከሰተውን ችግር ከማቃለል እና መፈትሄ ከመስጠት ይልቅ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚተጉ ድርጅቶች፣ የመገናኛ አውታሮች፣ አክትቪስቶች እና ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ እየጠይቅን በተለያዬ እርከን ላይ የሚገኙ የመንግስት ባለድርሻ አካላት፣ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች እና መላው የዐማራ ሕዝብ ችግሩ በተፈጠረበት አካባቢ አስቸኳይ ድጋፍ ለሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ እንዲያመቻች መዐሕድ ይጠይቃል፡፡
መዐሕድ የእልቂት መልክተኞችን በጥብቅ ያወግዛል፡፡ ይህንን ሰቆቃ ከበስተኋላ ሆነው ግፊት የሚያደርጉ እና የሚያበረታቱትን ማናቸውንም ኃይል አጥብቆ ይናኮንና።

ፈለገ አስራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!
የዐማራ ሕዝብ ትግል ያሸንፋል!

መዐሕድ
ጥር 07/ 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
……read in pdfAAPO Megilecha, 20191401- V2

Share this post